ነቶም ኣምሓሪኛ ቋንቋ ክርድኡ ዝኽእሉን፣ ንጉዳይ ኤርትራን ኢትዮጵያን ብንቕሓትን ምርምርን ክከታተሉ ዝደልዩ ግዱሳት ኤርትራውያንን ትግራዎትን ዝምልከት ኣገዳሲ ዓምዲ።
በ ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ ሰኔ 3 ፣ 2018

መግቢያ

ዶ/ር አቢይ አሀመድ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆነው ከተመረጡ በኋላ በተከታታይ ባወጣኋቸው ጽሁፎቼ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የአገራችን ችግሮች በሂደት ቀስ በቀስ መፈታት የሚችሉ እንጂ ከመቅጽበት ለመፈታት እንደማይችሉ ነው። አንዳንዶች ይህንን ዐይነቱን አቀራረቤን እንደ አድር-ባይነት በመመልከት የማያስፈልግ እንካስላንቲሃ ውስጥ ገብተዋል። እንደዚያ ዐይነት ጽሁፎች ስጽፍ በአገዛዞች መለወጥና መቻኮል በህዝባችን ላይ የደረሰውን ስቃይና የተሰራውንም የፖለቲካ ስህተትና ወንጀል ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እንጂ አቋሜን ከመቀልበስ ወይም አድርባይ አቋም በመያዜ አይደለም።

ዛሬም እንደትላንትናው የምታገለው ህዝባችን የተሟላ ዲሞክራሲ እንዲያገኝ፣ ሰላምን እንዲጎናጸፍና፣ ኃይሉን ሰብሰብ አድርጎ ሳይፈራ ሳይቸር በአንድነት በመነሳት አንድ ጠንካራ አገር እንዲገነባ ነው። በተለያዩ ጽሁፎቼ ላይ ለማመልከት እንደሞከርኩት፣ ዲሞክራሲ በየአራት ዐመቱ በሚደረግ ምርጫና በስልጣን ርክክቦሽ የሚገለጽ ብቻ ሳይሆን፣ በመሰረታዊ ፍላጎቶችም መሟላት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባለች ብዙ ነገሮችን ባላሟላች አገር ዲሞክራሲ ሰፋ ባለ መልኩ መታየትና ተግባራዊም መሆን ያለበት ጉዳይ ነው። ጠንካራ ኢኮኖሚ ሲገነባ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂም ሲዳብሩና ሲስፋፉ ዕውነተኛ ዲሞክራሲም ቀስ በቀስ ዕውን ሊሆን ይችላል። በተለይም በአገራችን ምድር ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዲገነባ የምንፈልግ ከሆነ በመጀመሪያ ደረጃና በቅድሚያ ተግባራዊ መሆን ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎችም የህውሃትን ወይም የወያኔን አገዛዝ የሚጠሉ የምንገነዘብ ይመስለኛል። ምርጫ ተካሂዶ የህዝቡ መሰረታዊ ፍላጎቶች እስካልተሟሉ ድረስ ስለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ማውራት አይቻልም። ከዚህም ባሻገር፣ በአንድ አገር ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ስር ሊሰድ የሚችለው ህዝቡ በንቃት ሲሳተፍና ትችታዊ በሆነ መንገድ የአገዛዞችን ፖሊሲዎች በመመርመር የበኩሉንም አስተዋፅዖ ሲያደርግ ነው።

በተለይም በአለፉት አስር ቀናት የአገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ ስንመለከት ነገሩ እንደምናስበው ተግባራዊ እየሆነ በመምጣት ላይ አይደለም። ርስበርሳቸው የሚቃረኑ ነገሮች እንደሚካሄዱ እንመለከታለን። በአንድ በኩል በአዲስ አበባ በአንዳንድ ቦታዎች ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ስለሰላም መስፈን ይነገራል፤ የአስተሳሰብ ለውጥም መደረግ እንዳለበት ይሰበካል፤ በሌላ ወገን ግን ወያኔዎች እዚያው በዚያው ግድያቸውን እንዳጧጧፉትና አልሞትንም፣ እንዲያውም ስልጣኑ በእጃችን ላይ ነው ያለው፤ አገርን የማጥፋት ዓላማችንንም ማንም ሊገታው አይችልም ብለው ይዝታሉ። በተለይም መቀሌ ተሰባስበው ግንቦት 20ን ሲያከብሩ የተናገሩትን ላዳመጠ እነዚህ ሰዎች አንድ የሚጎድላቸው ነገር አለ ብሎ ማሰቡ የማይቀር ነው። ከተለያዩና ቀና አመለካከት ካላቸው ኢትዮጵያውያን ጋር ቁጭ ብለን ስናወራ ሁላችንም የደረስንበት ድምዳሜ ወያኔዎች አንድ የጭንቅላት ችግር እንዳለባቸው ነው መገንዘብ የቻልነው።

                                                                      1

ያም ተባለ ይህ፣ የዶ/ር አቢይ አህመድ መመረጥ ጥሩ የሆነውን ያህል፣ በአንድ ወገን እዚያው በዚያው የሚወስዱት እርምጃዎች፣ በሌላ ወገን ደግሞ በአረጀ አስተሳሰብ መጓዝ አይቻልም፤ በተለይም የወጣቱን ችግር ለመፍታት የግዴታ ዘመናዊ አስተሳሰብ ያስፈልጋል እያሉ በሚናገሩት መሀከል አልፎ አልፎ አለመጣጣም ይታያል። በተለይም ከአንድ ሳምንት በፊት ከሳውዲ አረብያ ከተመለሱ በኋላ የሚሌኒዩም አዳራሽ ውስጥ ተገኝተው ያደረጉት ንግግር በአማዛኝ ጎኑ ጥሩ የሆነውን ያህል፣ እዚያው ስብሰባ ላይ ስለ አላሙዲን መፈታት ያደረጉትን ሙከራ መናገራቸውና፣ ከሞከሩም ትክክል እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው አላሙዲን ከፍተኛ ወንጀል የፈጸመና አገዛዙን እንዳለ ያባለገ ነው።የአገርን ሀብት በመዝረፍ ወደ ውጭ የሚያሽሽና አገርን ያራቆተ ነው። ስነ-ምግባር የሌለውና ለአንዳንድ ወጣቶችም መጥፎ ምሳሌ የሆነና የባህል ጠንቅ ነው። ስለሆነም የሱ መፈታት አለመፈታት የኢትዮጵያ ህዝብ አንገብጋቤ ጥያቄ አይደለም። በሁለተኛ ደረጃ፣ አዜብና አስመላሽ ወልደስላሴ የሜቴክ የቦርድ አባል ሆነው መመረጣቸው አብዛኛዎቻችንን ጥርጣሬ ውስጥ ከቶናል። ፖለቲካው ዘመናዊ አስተሳሰብና ድርጊት ያስፈልገዋል በሚባልበት ወቅት እነዚህን የሙስና እናትና አባት እንደገና ወደስልጣን ማምጣት ተሃድሶ ሳይሆን የኋሊት ጉዞ ነው የሚመስለው። ከዚህ በመነሳት የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮች ቀስ በቀስ ለመፍታት በቅድሚያ መወሰድ ያለባቸውን ነገሮች አጠር አጠር ባለመልክ ላቀርብ እወዳለሁ።

የብሄራዊ ዕርቅ ጉዳይና የአገራችን የተወሳሰቡ ችግሮች !

በብሄራዊ ዕርቅ ጉዳይ ላይ የተሻለ ግንዛቤ አለን የሚሉና ለአገራችንም የተወሳሰቡ ችግሮች መፍትሄ ብሄራዊ ዕርቅ አማራጭ የሌለው የመጀመሪያው ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለው የሚወተውቱ ግለሰቦች ጠለቅ ብለው የማያብራሯቸው መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ። በአገራችንም ሆነ በአንዳንድ አምባገነናዊ ወይም ፋሺሽታዊ አገዛዞች በሰፈኑባቸው አገሮች ውስጥ አገዛዞችን በመቃወም የጦር ትግል ሲካሄድ ወይም ውዝግብ ሲነሳ ለዚህ ዐይነቱ የርስበርስ ጦርነት ዋናው ምክንያት የሚሆኑት የጭቆናን ስርዓት የሚያሰፍኑት ራሳቸው አገዛዞችና፣ እንደዚህ ዐይነቱን አገዛዞች የሚደግፉ የውጭ ኃይሎች ናቸው። ጦርነቱና ውዝግቡ እየተባባሰ ሲሄድ የብሄራዊ ዕርቅ አማራጭ እንደሌለው ነገር ቢታይም፣ ይህ ዐይነቱ ጉትጎታ በተለይም ስልጣን ላይ ላሉት ስትንፋስ መስጫና ኃይልን መሰብሰቢያና ማጠናከሪያ ጊዜ ሊሆን ይችላል።

በታሪክ ውስጥ የብሄራዊ ዕርቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የሆነው ከሰላሳ ዓመቱ የሃይማኖት ጦርነት በኋላ በዌስት ፋሊያው ስምምነት በ1648 ዓ.ም ላይ ነው። ጦርነቱ ወሰንን ያለየ የፕርቴስታንና የካቶሊክን ሃይማኖት በሚከተሉ መሀከል የተካሄደ ነው። በአንዳንድ ቦታዎች ሁለትሶስተኛው የሚሆነው ህዝብ አልቋል። የጦርነቱ ምክንያት ሃይማኖት ነው ቢባልም ዋናው መነሻው ግን የስልጣን ጉዳይ ነው። ጦርነቱም ጋብ ሊልና ወደ ስምምነትም ሊደረስ የተቻለው፣ በአንድ በኩል በተለይም አራሹ ገበሬ በጦርነቱ የተነሳ በብዛት በመሞቱና አራሽም በመጥፋቱ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የጦርነቱን አሰቃቂነት የተከታተሉ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች የማያቋርጥ ውትወታና የዕርቅ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ሌት ተቀን በመስራታቸው ነው። ከዚህ ጦርነትና 2

ስምምነት በኋላ ነው የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ቀስ በቀስ ብሄራዊ ኢኮኖሚ በመገንባት ለህብረ-ብሄር ምስረታ መሰረት የጣሉት።

ወደ አገራችን ስንመጣ የወያኔን አነሳስ ታሪክና ባለፉት 27 ዐመታት ተግባራዊ ያደረጋቸውን ፖሊሲዎች የሚመስሉ ነገሮችን ስንመለከት ዋና ዓላማው የራሱንና የውጭ ኃይሎችን የበላይነት ለማስፈን ብቻ ነው። ይህም ማለት ህወሃት እስከዛሬ ድረስ በአገራችን ምድር ያካሄደውና የሚያካሄደው ፖሊሲ በአንዳች ርዕዮተ-ዓለም ላይ የተመሰረተ ወይም ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ሳይሆን፣ „ፍልስፍናው“ ጥላቻ፣ ቂም-በቀል፣ ስግብግብነትና ስልጣን ብቻ ናቸው። ከዚህ ውጭ ወያኔ የሚያምንበት አንዳችም ርዕዮተ-ዓለም የለውም። አብዮታዊ ዲሞክራሲንና ልማታዊ መንግስትን እንደ ርዕዮተ-ዓለምና እንደ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መመሪያ አድርጎ በመውሰድ አገዛዙን በመወንጀል የማይሆን ግብግብ ውስጥ መግባት የችግሩን ዋና ምክንያት እንዳንረዳ ያደርገናል።

ከዚህ ስንነሳ ወያኔ በውጭ ኃይሎች እየተመከረና እየታገዘ የአገራችንን ሀብት ለመቆጣጠር ኢፈርትንና ሜቴክ የሚባሉትን ድርጅቶች በማቋቋም የፈረጠመ አገዛዝ ነው። በእነዚህ ሁለት ድርጅቶች አማካይነትም ከበታቻቸው ያሉ ተቀጥያና ተቋራጭ የሆኑ (Sub-Contractors) ኩባንያዎችን በመክፈት በአንድ በኩል ሀብት እየዘረፈ ነው፤ በሌላ ወገን ደግሞ ተወዳደሪ እንዳይፈጠር በማድረግ የአገራችን ኢኮኖሚ ሰፋ ባለ መሰረት ላይ እንዳይገነባ መንገዱን የዘጋ ነው። ስለሆነም በጉልበት የነጠቀውንና በኒዎ- ሊበራሊዝም የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ህጋዊ ያደረገውን የሀብት ዘረፋ ላለማስነጠቅ ሲል የተወሳሰበ የጭቆናና የአፈና መዋቅር ዘርግቷል። በተለይም ከምርጫ 1997 በኋላ የባሰ ጨቋኝ እየሆነ ሊመጣ የቻለው በውጭ ኃይሎች በመደገፍና የስለላ መዋቅሩን ለማጠናከር ምክርም ስለተሰጠው ነው። የውጭ ኃይሎችም የአገራችን ቆንጆ ሙዚቃዎችና ባህሎች፣ እንዲሁም የተለያዩ ብሄረ-ሰቦችና ሃይማኖቶችም የብሄራዊ አንድነት ምልክቶቻችን መሰረቶች አድርገው በመቁጠራቸውና፣ እነዚህም ለጠንካራ ህብረ-ብሄር ምስረታ ይጠቅማሉ ብለው ስለሚያስቡ ከአገዛዙ ጋር በማበር እነዚህ እሴቶች እንዲበጣጠሱና የእርስ በርስ ጦርነት እንዲነሳ ያላደረጉትና የማያደርጉት ሙከራ ይህ ነው አይባልም። ወያኔ ይህንን የውጭ ኃይሎችን አደገኛ ዓላማ አስፈጻሚ በመሆኑና፣ የነሱንም ድጋፍ እስካገኘ ድረስ ብቻ ስልጣን ላይ የሚቆይ ስለሚመስለው የተወሳሰበውን ችግር ከፖለቲካ አንፃር በገምገምና ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ በማጤን ብሄራዊ ዕርቅ ለማድረግ ዝግጁ አይደለም። የሚፈልግ ቢሆን ኖሮ እስከዛሬ ድረስ በሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ባልቀጠፈ ነበር።

አብዛኛውን ጊዜ ብሄራዊ ዕርቅ አስፈላጊ የሚሆነው በአንድ አገር ውስጥ የሚደረግ ትግል በርዕዮተ-ዓለም ዙሪያ የሚካሄድ ከሆነና፣ ይህ ዐይነቱ ጦርነት ወይም ትግል ለብሄራዊ ደህንነት ጠንቅ መሆኑ ግንዛቤ ሲኖር ነው። በተለይም ርዕዮተ-ዓለምን ተገን አድርጎ ጭቆናዊ አገዛዝን ያሰፈነ ኃይል ነገሩ ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ ሲሄድ ራሱ የገዢው መደብ የሁኔታውን ውስብስብነት በመረዳት አይ ወደ ብሄራዊ ዕርቅ ይመጣል፤ አሊያም ደግሞ ሜዳውን ለምርጫ ልቅ ያደርጋል። ስለሆነም ባለፉት ሰላሳ ዐመታት በተለያዩ አገሮች ብሄራዊ ዕርቅ ተግባራዊ ሆኗል። ይሁንና ግን ብሄራዊ ዕርቅ ቀድሞ የተዘረጋውን የኃይል አሰላለፍ፣ የሀብት ክፍፍልና ቁጥጥር ሊለውጥ እንደማይችል ብሄራዊ ዕርቅ የተደረገባቸው አገሮች ያረጋግጣሉ። በአንዳንድ አገሮች በየአራት ዐመቱ ምርጫ ቢካሄድም እዚያው በዚያው ደግሞ ኢ-ፍትሃዊ አገዛዝ ስር እንደሰደደ፣ ስራና መኖሪያ የሚፈልገውም ዕድል ሳያገኝ እንደሚሰቃይና ወደሌላ አገር እንደሚሰደድ እንመለከታለን።

                                                                                  3

ይህ የሚያሳየን ምንድነው ? ብሄራዊ ዕርቅ ወይም አንዳች ዐይነት ምርጫ በአንድ አገር ውስጥ ስር የሰደዱ፣ በተለይም በኢኮኖሚና በማህበራዊ የሚገለጹ ኢ-ፍትሃዊ ሁኔታዎችን በፍጹም እንደማይፈቱ ወይም እንደማያቃልሉ ነው የምንገነዘበው። ምርጫ ከተካሄደና የወታደር አገዛዞች ወደ ካምፓቸው ከተመለሱ በኋላም ጭቆናዊና ኢ-ፍትሃዊ አገዛዝ በድሮ መልካቸው ይቀጥላሉ። እንደ ብራዚል፣ አርጀንቲናና ቺሌ፣ እንዲሁም በተቀሩት የላቲን አሜሪካ አገሮች ውስጥ የወታደር አገዛዝ ለመመለስ የሚችልበትም ሁኔታ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል። በተለይም ብራዚል ውስጥ ከፍተኛ አለመረጋጋት ሲኖር፣ በተጨባጭ ከበስተጀርባ ሆነው አገሪቱን የሚገዙት የመሬት ከበርቴዎችን ጥቅም የሚያስጠብቁ ወታደሮች፣ የደህንነት ስዎችና ፓራ-ሚሊተሪ የሚባሉ ደሃውንና በስርቆት የሚጠረጥሩትን አነጣጥረው የሚገሉ ናቸው።

ስለሆነም ድሮም ሆነ ዛሬ በብሄራዊ ዕርቅና በሰላም ዙሪያ የሚደረገው ቅስቀሳ አዘናጊና እጅግ አደገኛ የሚሆነው፣ በአንድ በኩል በአገራችን ውስጥ የሰፈነውን ጨቋኝ ስርዓትና የኢኮኖሚና የማህበራዊ መሰረቱን ያላገናዘበ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የውጭ ኃይሎችን ሚና ቁጥር ውስጥ ያስገባ አይደለም። ይህ ዐይነቱ በአገዛዙና በውጭ ኃይሎች ያለው መተሳሰር ደግሞ ለሰላም፣ ለብሄራዊ ዕርቅ፣ ለተስተካከለና ለሁለ-ገብ ዕድገት የሚያመች አይደለም። ከዚህ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ስንነሳ ለዲሞክራሲና ለዘላቂ ሰላም የሚደረገው ትግል በምን መልክ ነው መካሄድ ያለበት ? የሚለው ነው ግራ የሚያጋባን። ዶ/ር አቢይና አማካሪዎቻቸው ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ በማጤን መፍትሄ ለመፈለግ ስትራቴጂ ይቀይሱ አይቀይሱ የምናውቀው ነገር የለም። ማለት የሚቻለው ወደፊት በሚከተሉት የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ የሳቸውን አቋምና ሚና በተሻለ መንገድ ልንገነዘብ እንችላለን። በሌላ አነጋገር፣ ወያኔ እስካሁን ተግባራዊ ካደረገው በዓለም ኮምኒቲው ከሚደገፈው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይላቀቁ ወይስ አይላቀቁ በግልጽ የምናውቀው ጉዳይ የለም። ቢያንስ በዚህ ላይ ግልጽ አቋም ሲኖረቸውና የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸውን በይፋ ስናውቅ የወደፊት ጉዞአቸውንም ለመረዳትም ሆነ ትንተና ለመስጠት እንችላለን።

የተሟላ ሰላም ማስፈን ሊታለፍ የሚገባው ጉዳይ አይደለም !!

በካፒታሊስት አገሮች አነሳሺነት በአገሮች መሀከል ወይም በአንድ አገር ውስጥ የርስ በርስ ግጭት ሲፈጠር ጦርነቱን ለማቆም ሲባል ተቃራኒ ኃይሎች ይጋበዛሉ። ውይይት ይደረጋል፣ ወርክሾፕም ይዘጋጃል። ከአገራችንም ሆነ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ወጣቶች እየተጋበዙ በመምጣት ስለሰላም አስፈላጊነትና ስለ ጠብ መፍቻ ዘዴ(Conflict Resolution Method) ትምህርት ይሰጣቸዋል። ይሁንና ግን በምዕራብ አውሮፓ መንግስታት አነሳሺነት በሚካሄደው የሰላምና የዕርቅ ስብሰባ ላይ በዋናው ምክንያት ላይ ጠለቅ ያለ ውይይት አይካሄድም። ለሰላም አለመኖር ምክንያት በሆኑት ነገሮች ላይም ውይይት ስለማይደረግ የሚቀርበውም መፍትሄ ችግሩን ውስብስብ የሚያደርግና የነፃነትንና የዕውነተኛ ዲሞክራሲ ጥያቄዎችን የማይመልስ ነው። የምዕራብ አውሮፓ

መንግስታትና አሜሪካ ለሰላም እጦት በዋናነት መጠየቅ የሚገባቸው ቢሆኑም ከደሙ ንጹህ እንደሆኑ ነው ሰውን ለማሳመን የሚሞክሩት። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ጣልቃ በመግባትና አሸባሪዎችን በማስታጠቅ የመንግስት ለውጥ(Regime Change) ለማምጣት በሚያደርጉት ሙከራ የብዙ ስዎች ደም እንደሚፈስና ለዚህም ተጠያቂ ለመሆናቸው በይፋ አይናገሩም።

                                                                                             4

በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተዘረጋው ዓለም አቀፋዊ የሚሊቴሪ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተቋም፣ እንዲሁም ደካማ አገሮችን የማይሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲከተሉ በማድረግና የመጨቆኛ መሳሪያዎቻቸውን እንዲገነቡ በማስገደድ በየአገሮች ውስጥ ለሰላም እጦትና ለኢ-ፍትሃዊ አገዛዝ መሰረት ጥለዋል። በመሆኑም የአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች መንግስታት ዋና ተግባር ወደ ጦርነትና ጨቋኝነት በመለወጥ ዕውነተኛ ሀብት እንዳይዳብር ተደርጓል። አገዛዞች አትኩሮአቸው በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲያዘነበል በመደረጉ አንድን ህብረተሰብ ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን ትክክለኛ ዕውቀት እንዳይቀምሱ ተደርገዋል። አብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም መንግስታት የፖለቲካ ግንዛቤ(Political awareness)፣ የማህበራዊ ግንዛቤ(Social awareness)፣ የኢኮኖሚ ግንዛቤ(Economic awareness)፣ ባህላዊ ግንዛቤ(Cultural awareness)፣ ታሪካዊ ግዴታና ግንዛቤ(Historiacl obligation and awareness) የመሳሰሉትን ለአንድ ህብረተሰብ የሚያስፈልጉ መሰረተ-ሃሳቦችን ከመንፈሳቸው ጋር ያዋሃዱ ባለመሆናቸው እራሳቸውን ከአገርና ከህዝብ በላይ አድርገው በመቁጠር የአንድ ትውልድ ዕድል ብቻ ሳይሆን የሶስትና የአራት ትውልድን ዕድል ያበላሻሉ። ከዚህም በላይ የሚመሩበት ዕምነትና ደንብ(Principles)፣ ስለሌላቸውና፣ በቲዎሪ፣ በሳይንስና በፍልስፍናም ያልታጠቁ በመሆናቸው የዓለም አቀፍ ኮምኒቲውን ትዕዛዝ በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ በቀላሉ ሊፈታ የማይችል ህብረተሰብአዊ ጉዳት አድርሰዋል፤ እያደረሱም ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ከተማዎችና መንደሮች በስርዓት እንዳይገነቡ፣ የስራ- ክፍፍል እንዳይዳብርና ሰፋ ያለ የገበያ መዋቅር ተዘርግቶ ወደ ዕውነተኛ ህብረ- ብሄር(Nation-State) እንዳይሸጋገሩ በቀላሉ ሊወገዱ የማይችሉ መሰናክሎች ተተክለዋል። በተለይም በግሎባላይዜሽንና በነፃ ንግድ ዘመን የሶስተኛው ዓለም አገሮች የቆሻሻ መጠያ በመሆን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ኑሮ ተምታቶባቸዋል፤ የኑሮን ትርጉም እንዳይረዱ ተደርገዋል። ይህ ዐይነቱ በየአገሮች ውስጥ የሰፈነው እጅግ የሚያሳዝን ሁኔታ በየአገሮች ውስጥ ለሰላም እጦት ምክንያት ሊሆን ችሏል።

ወደ አገራችን ስንመጣ በአገራችን ውስጥ ለሰፈነው አለመረጋጋትና የሰላም እጦት ዋናው ምክንያትና ተጠያቂው የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን አገዛዙ ነው። እስከአፍጢሙ ድረስ በመታጠቅና ሰላማዊ ህዝብን የሚያስፈራራና አልፎም የሚገድል ተራው ህዝብ ሳይሆን የራሱን ህገ-መንግስት የሚጥሰው ያልሰለጠነው የወያኔ አገዛዝ ነው። ስለሆነም ስለሰላም አለመኖርና ስለሰላምም አስፈላጊነት በሚወራበት ጊዜ ዋናውን ምክንያት የግዴታ እያነሱ መወያየት መፍትሄ እንድንሻ ያስችለናል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ለአንድ ዋና ምክንያት ከበስተጀርባው ሌላም ምክንያት ስለሚኖር በአንድ አገር ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ በግልጽ ከሚታዩ ነገሮች ባሻገር በመሄድ መመርመር ያስፈልጋል። በዚህ መልክ ብቻ ወደ ተጠጋጋ መፍትሄ ላይ ለመድረስ ይቻላል።

ወደ ተግባራዊ ነገሮች ስንመጣ እንደሌሎች መሰረታዊ ነገሮችም ሰላም ተቀዳሚውና ተግባራዊ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው። ካለውሃ፣ ካለምግብ፣ ካለ መጠለያና ካለንጹህ አየር ለመኖር የማንችለውን ያህል፣ በአንድ አገር ውስጥ ሰላም እስካለሰፈነ ድረስ አንድ ሰውም ሆነ ህዝብ ሃሳቡን በመሰብሰብ አዳዲስ ነገሮችን ሊፈጥርና አንድ ነገር ሰርቶ ውጤታማ ነገር ማየት አይችልም። በግልጽ እንደምናውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት አርባ ዐመታት በሰላም እጦት የሚሰቃይና፣ ከፍተኛ የህሊና መቃወስ የደረሰበት ህዝብ ነው።

                                                                                       5

 እስከዛሬም ድረስ ባለፈውና በዛሬው አገዛዝ ምንም ጥፋት ሳያጠፋ ጠበንጃ ይዘው በሚንጎራደዱና ሲዞርባቸው ጠበንጃቸውን በመቀሰር በሚያስፈራሩና መንግስት በሚባል ኃይል በሚታዘዙ በፍርሃት ዓለም ውስጥ እንዲኖር የተገደደ ነው። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ተፈጥሮአዊ ሳይሆን ሰው ሰራሽና የአንድን ህዝብ ነፃነት የሚገፍ ነው። ለመሆኑ ለሰላም እጦት ከምናየው ነገር ባሻገር ሌላው ምክንያት ምንድነው? ብለን እንጠይቅ ይሆናል ። አብዛኛዎቻችን እንደዚህ ዐይነቱን ጉዳይ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ጋር ብቻ እናያይዛለን። በእኔ እምነት በቂ ወይም የተሻለ መልስ ለማግኘት የግዴታ ከዚህ ተሻግረን መሄድ ያለብን ይመስለኛል።

በሌሎች መጣጥፎቼ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የዛሬውን አገዛዝ ውስጣዊ ባህርዮች በርዕዮተ-ዓለም የምንገልጻቸው ሳይሆኑ በሌላ መልክ ብቻ ነው። ስግብግብነትና ስልጣን(Greed and Power)የአገዛዙ ባህርዮች ሲሆኑ፣ ከዚህም ባሻገር ቂም-በቀልነትና የዝቅተኛነት ስሜት አንድ ላይ በመደባልቅ አገዛዙን ሰላም ነሽ አድርገውታል። አብዛኛውን ጊዜ ለጦርነት ወይም ለሰላም እጦት ዋናው ምክንያት የዝቅተኛነት ስሜትና የበላይነት ስሜቶች ከስልጣን ጋር የተያያዙ እንደሆን ነው። የዝቅተኛነት ስሜት ያላቸው በታሪክ አጋጣሚ አንድ ላይ በሚሰባሰቡበት ጊዜ ግለሰብአዊ ኃይላቸውን በማቀናጀት የተደበቀውን የቂም በቀል ባህርያቸውን ወደ ውጭ በማውጣት ለሰላም እጦት ምክንያት ይሆናሉ። የዝቅተኝነት ስሜት ደግሞ ከአዕምሮ መዛባት ወይም ተኮትኩቶ ካለማደግ ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ የሆነ አጋጣሚ በሚያገኝበት ጊዜ የተበላሸ ውስጣዊ ስሜቱን ወደ ውጭ በማውጣት ለሰላም እጦት ምክንያት ይሆናል። በዚህ ላይ ሀብትና በመሳሪያ ላይ የተመረኮዘ ኃይል ሲደመሩበት የዝቅተኝነትና የቂም-በቀል ስሜቱ በማየል ለረጅም ጊዜ የሰላም እጦት ምክንያት ይሆናል። ከዚህ ባሻገር ወያኔዎች የፈለቁበት ማህበረሰብ በስራ-ክፍፍልና ሰፋ ባለ የህብረተሰብአዊና የምሁራዊ እንቅስቃሴ ያልዳበረና ከሌላውም የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያልተቀላቀለ በመሆኑ አስተሳሰባቸው በጣም ጠባብና በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ ነው። ሰለሆነም ተጨባጭ ሁኔታዎችን፣ የታሪክን ሂደትና የህብረተሰብን አገነባብ ታሪክ በተሳሳተ መልክ የሚረዱና የሚያነቡ ናቸው። እንደዚህ ዐይነቱን ችግር በማባበል፣ ወይም ብሄራዊ ዕርቅ እናድርግ እያሉ በመወትወት የሚፈታ አይደለም። በሌላ ወገን ግን ከእንደዚህ ዐይነቱ እልከኛና በቂም-በቀል ከተወጠረ ኃይል ጋር ፊት ለፊት መጋፈጡ በቀላሉ ሊፈታ የማይችል ሁኔታ ውስጥ ሊከትን ይችላል። ለዚህ መፍትሄው የተሰበጣጠረ ትግል ሳይሆን በሳይንስና በፍልስፍና ላይ፣ እንዲሁም በቲዎሪ ላይ የተመረኮዘ የተቀነባበረ ትግልና ሰፋ ያለ ህዝባዊ ተቃውሞና ምሁራዊ ትግል ብቻ ነው ዋናው መፍትሄ። አንድ ህዝብ ሰላም አጥቶ መኖር እንዳይችል ከተደረገ ከዳር እስከዳር በመንቀሳቀስ የግዴታ አገዛዙን መጋፈጥ ያስፈልጋል። በምሁራዊ ዕውቀትም ህዝቡን በማንቃትና ለመብቱ እንዲታገል በማድረግ የአገዛዙን መዋቅር በማንኮታኮት ለአዲስ ስርዓት መታገል ያስፈልጋል።

ሌላው ለሰላም አለመኖር ምክንያት ደግሞ ከበላይነት ስሜት ጋር የሚያያዝና ኢ- ፍትሃዊ አገዛዝን የሚያሰፍን ነው። እነዚህኞቹ ራሳቸውን ከሌላው ሰው ጋር ሲያወዳደሩ የተለየን ፍጡሮች ነን ብለው ስለሚያምኑ ለሰላም እጦት ምክንያት ይሆናሉ። በተለይም በዚህም በዚያም ብለው ሀብት በማካበት ላቅ ያለ ኑሮ የሚኖሩ በአካባቢያቸው ሰላምን ሊነሱ ይችላሉ። ከዚህ በተረፈ የበላይነት ስሜት ከዘረኝነትም ጋር የሚያያዝና ከሌላው የተሻልኩኝ ነኝ የሚለው የራሱን ቆዳ ወይም ቀለም የተሻለ አድርጎ በመቁጠር በሌሎች ላይ የበታችነት ስሜት እንዲያድር ያደርጋል።

                                                                                  6

ይህ ዐይነቱ የበላይነት ስሜት ከባሪያ አገዛዝ ጀምሮ የቅኝ-አገዛዝን አቆራርጦ በዳበረው የካፒታሊዝም ስርዓት(Monopoloy Capitalism or Imperialism) ውስጥ በመስፋፋትና ዓለም አቀፍ ባህርይን በመውሰድ ሌሎች የሶስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ አገሮች የጥሬ-ሀብት አምራቾች ብቻ ሆነው እንዲቀሩ ያደረገ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ በየአገሩ ያሉ ኤሊቶች ከእንደዚህ ዐይነቱ ኃይል ጋር በማበርና ሀብትን በመበዝበዝ፣ በዚያው መጠንም ኢ-ፍትሃዊ አገዛዝና የዝቅተኝነት ስሜት በመስፋፋት በየአገሩ ውስጥ ውዝግብ ሊፈጠር ችሏል። ከዚህ ባሻገር ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኮሪያ አንስቶ እስከቬትናምና አንጎላ ድረስና፣ እንዲሁም ሞዛምቢክና ሌሎች አፍርካ አገሮች የተካሄዱትና የሚካሄዱት ጦርነቶች በተለይም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጣልቃ-ገብነት ሲሆን፣ ሌሎች ጦርነቶች ደግሞ የውክልና ጦርነቶች(Proxy War) ናቸው። ይህም ማለት በብዙ አካባቢዎች የሚካሄዱት ጦርነቶችና በየአገሮች ውስጥ ደግሞ ኢ-ፍትሃዊና የጭቆና አገዛዝ ሰፍኖ ህዝቦች በሰላም እንዳይኖሩ ማድረግ በቀጥታ ከውጭ ኃይሎች ጋር የተያያዘ ነው። በአገራችንም የተዘረጋው እ-ፍትሃዊ አገዛዝና ጭቆና እንዲሁም ሰላም ማጣት የውጭ ኃይሎች በአገራችን ውስጥ የፈለጉትን እንዲያደርጉ በሩ ስለተከፈተላቸውና ሰፋፊ መሬት ተሰጥቶአቸው ኢምባሲዎቻቸውን እንዲያቋቁሙ ስለተፈቀደላቸው ነው። ይህንን ልዩ ጥቅም(Privilege) በመጠቀም ከውስጥ ሆነው በአገራችን ምድር ሰላም እንዳይኖሮ የአገራችንን ዜጎች በስለላ በማስልጠን ወንጀል ፈጽመዋል፤ እየፈጸሙም ነው።

ዛሬ እንደምናየው ከሆነ፣ በአንድ በኩል ዶ/ር አቢይ ስለሰላም ጥሪ ሲያደርጉ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ህዋሃትና ካድሬዎቹ ሰላም እንዳይሰፍን ከበታች ሆነው ስራቸውን ይሰራሉ። በአንድ በኩል ራሳቸው ስለ እርቅ እያወሩና በየሆቴል ቤቱም ንግግርና ክርክር እየተደረገ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በአዲስ መልክ በመሰባሰብ በአዲስ ስትራቲጂ ሳይሆን ያንኑ ያረጀ ዘዴያቸውን በመጠቀም አንዳንድ የዋሁን ኢትዮጵያዊ በማታለልና በገንዘብ በመግዛት ሰላም እንዳይኖር የማይሸርቡት ተንኮል ይህ ነው አይባልም። ይህ ዐይነቱ ተንኮል በጄኔራል ቪዴል ይመራ የነበረውን የአርጀንቲናን የፈሺሽት ገዚዎችን ድርጊት ያስታውሰኛል። በ1978 ዓ. ም በአርጀንቲና የዓለም ኳስ ጨዋታ ውድድር የመክፈቻ ንግግር ላይ ጄኔራል ቪዴል አርጀንቲናና የአርጀንቲና ህዝብ ሰላም እንደሚፈልጉና ለዚህም እንደሚጸልዩ፣ እግዚአብሄርም ከጎናቸው እንደቆመ ነበር የተናገረው። ይሁንና ግን የኳስ ጨዋታው ውድድር በመካሄድ ላይ እያለ በዚያው ዕለትና በተከታታዩ ሳምንታት ጁንታዎቹ ተራማጅ ነው ብለው የሚጠረጥሩትን ወጣትና የተማረ ኃይል ሁሉ ያድኑና ይገድሉ፣ የተቀሩትን ደግሞ ያስሩ ነበር። ወያኔም የሚያደርገው ይህንን ነው። ስልጣንም ሙሉ በሙሉ ከእጁ ከወጣ ትግራይ ያሸሸውን ጦርና ታንክ፣ እንዲሁም አውሮፕላኖች በማንቀሳቀስ ጭፍጨፋ ለማካሄድ ዝግጁ እንደሆነ እየዛተ ነው።

ከዚህ ባሻገር ሰላም እንዳይኖር ወይም እንደ ይጎዝላቪያ ዐይነት የርስ በርስ መተላለቅ እንዲፈጠር የውጭ ኃይሎች የስለላ ድርጅቶች ሁኔታውን ለማቀጣጠልና ልዩ ዐይነት ውስጠ-ኃይል እንዲኖረው ስራቸውን እየሰሩ ነው። ታዲያ በእንደዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ እስከመቼ ድረስ ነው መቆየት የሚቻለው? ሌሎች ነገሮችን ተግባራዊ ለማድረግ ጊዜን የሚጠይቁ ቢሆንም የሰላም መስፈን ለአንድ ህዝብ እንደ ንጹህ ውሃና ምግብ እንዲሁም የሚተነፍሰው አየር እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ለሰላም ጠንቅ የሆኑ የጭቆና መሳሪያዎች እስካሉ ድረስና፣ የውስጥ ለውስጥ ትንኮል የሚሸረብና ሰውም የሚገደል እስከሆነ ድረስ ሰላም ሰፋኗል ብሎ ማውራት በፍጹም አይቻልም።

                                                                                         7

 ከዚህ ስንነሳ ለሰላም መስፈን ጠንቅ የሆኑ ነገሮችን በሙሉ በማጥናት ከስር መሰረታቸው እንዲነቀሉና ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ እንዲወድሙ ማድረግ ለአገር ግንባታ ቅድመ-ሁኔታ ነው። ይህም ማለት፣ ቢያንስ ለጭቆናና ለግድያ ምክንያት የሆኑ ነገሮች በሙሉ መወገድ አለባቸው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ለሰላም ጠንቅ የሆኑ ሰዎችና ተንኮል የሚሸርቡ ከስልጣን አካባቢ መወገድ አለባቸው። ህዝቡ ሳይፈራና ሳይቸር የሚንቀሳቀስበት፣ በሰላም ወጥቶ በሰላም ወደቤቱ የሚመለስበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። በተጨማሪም ለሰላም እጦትና ለኢ-ፍትሃዊ አገዛዝ ምክንያት የሆኑ የተዘረፉ የህዝብ ሀብቶች ቀስ በቀስ የህዝብ የሚሆኑበትና በአውቶነመስ ደረጃ በዘመናዊ የማናጀሜንት ቴክኒክና የንግድ መስተዳደር በመካሄድ በቀለጠፈ መልክ የሚሰሩበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት። በአንድ አገርና በዚያ አገር ውስጥ የሚገኙ ሀብቶች የጥቂት ግለሰቦች ሀብት መሆን የለባቸውም። አንድ ሰው ወይም በድርጅት የተደራጀ ራሱ ሰርቶ የሚያዳብረው ሀብት እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው የየግለሰቡ ወይም የድርጅቱ ሀብት ሊሆን የሚችለው። ይህም ማለት፣ የአንድ ሰውም ሆነ የድርጅት ሀብት በስራ ላይና በፈጠራ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት እንጂ በዘረፋ ላይ የተመሰረተ መሆን የለበትም። ስለሆነም ጥቂቶች በጉልበት የህዝብን ሀብት በመንጠቅና በመደለብ በመቶ ሚሊዮን ህዝብ ላይ የመፍረድና የማሰቃየትም መብት ሊኖራቸው አይገባም።

ከዚህ በመነሳት ሰሞኑን ከየቦታው የሚሰማው እሮሮ የዶ/ር አቢይ አህመድ መመረጥ ጥሩ የሆነውን ያህል፣ በሌላ ወገን ሰፊው ህዝብ ትጥቁን እንዲፈታና እንዲዘናጋ እየተደረገ ነው። በየሆቴል ቤቱም የሚደረገው ክርክርና ውይይት የነሱን ቀልብ የሳበ አይደለም። ለዶ/ር አቢይ ጊዜ የመስጠቱ ጉዳይ አስፈላጊ የሆነውን ያህል፣ የእነ አዜብ መስፍን እንደገና ከፍተኛ ቦታ ማግኘት እንድንጠራጠር ያደርገናል። ዶ/ር አቢይ ከምን ስሌት በመነሳት እነ አዜብን እንደገና ለስልጣን እንዳበቋቸው ከጥርጣሬ በስተቀር የምንሰጠው በቂ ምክንያት የለም። የምናሳስበው ነገር ቢኖር እንደነዚህ ዐይነቱ በስልጣንና በስግብግብነት የሰከሩና በልተው የሚጠግቡ የማይመስላቸው ኃይሎች ከተወገዱ በኋላ ጥሩ ስራ እንደሰሩ እንደገና እንዲመለሱ ማድረጉ ከሰላም ሎጂክ ጋር የሚጣጣም አይደለም። የምናወራው ስለ አገርና ስለ መቶ ሚሊዮን ህዝብ ዕጣና ስለተከታታዩም ትውልድ ዕድል እስከሆነ ድረስ ለዘላቂ ሰላም የሚሆኑ መሰረቶች ቀስ በቀስ መዘርጋት አለባቸው። ምክንያቶቹ ከስር መሰረታቸው መፈንቀል አለባቸው። ይህ ሲሆን ብቻ አንድ እርምጃ ወደፊት መራመድ እንችላለን ማለት ነው።

የዲሞክራሲ ጥያቄዎች መፈታት አስፈላጊነት !!

የዲሞክራሲም ጥያቄ ከሰላም መስፈን ጋር የተያያዘና የሚያያዝ ነው። ዲሞክራሲና ነፃነት ተግባራዊ በማይሆኑበት አገር ውስጥ ስለሰላም መስፈን ማውራት በፍጹም አይቻልም። ዲሞክራሲ በገዢዎች ፈቃድ የሚሰጥ ሳይሆን በትግል የሚገኝ ነው። በብዙ አገሮች ህገ-መንግስቶች ውስጥ የዲሞክራሲያዊ መብቶችን አስፈላጊነትና ተግባራዊ መሆን የተጻፉ ቢሆንም ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንደተነጠቁ እንመለከታለን።

                                                                                       8

በራሳቸው በካፒታሊስት አገሮችና፣ በተለይም በአሜሪካን ምድር ከተራው ዜጋ ይልቅ ጠበንጃ ይዘው በመኪና የሚዘዋወሩ ፖሊሶች የበለጠ መብት አላቸው። በዘረኛነት ስሜት በመነሳሳት ወጣት ልጆች ሳይቀሩ የማይሆን ምክንያት በመስጠት ይገዳላሉ። በወንጀልም የመጠየቅ ዕድላቸው በጣም የመነመነ ነው። ስለሆነም የዲሞክራሲ ጥያቄ የማያቋርጥ ትግልን የሚጠይቅና ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እስከሚሆን ድረስ ረጅም ጊዜ እንደሚፈጅ ነው። ይሁንና ግን በታሪክ ውስጥ እንደተረጋገጠው የዲሞክራሲ መብቶች ተግባራዊ መሆን አንድ ህዝብ በራሱ ላይ ዕምነት እንዲኖረው ያደርጋል። የፈጠራ ችሎታውን ያዳብራል። ህብረተሰብን የበለጠ ያስተሳስራል። ለዕድገት የሚያመች እንጂ የሚያደናቅፍ አይደለም። የዲሞክራሲ መብቶች ከኢንስቲቱሽኖች መገንባት ጋር ሲያያዙ ለአንድ ህዝብ የበለጠ ውስጣዊ-ኃይል ይሰጡታል። ህዝቡ ራሱን በሚገባ ለመግለጽና ሃሳብን ለማንሸራሸር ይረዳዋል። ዲሞክራሲ መንግስትን መቆጣጠሪያ መሳሪያ ሲሆን፣ አንድ አገዛዝ የህብረተሰብን ደህንነትና ሰላም የሚያናጉ ከህገ- መንግስቱ ውጭ የሆኑ ድርጊቶችን እንዳይፈጽም መቆጣጠሪያና መግቻ መሳሪያም ነው።

ወደ አገራችን ስንመጣ ለዲሞክራሲያዊ መብቶች ትግል ሲካሄድ ወደ 70 ዓመት ሊጠጋው ነው። በተለያየ የታሪክ ወቅት የተነሱ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች በአገዛዞች ፍርሃትና ፈቃደኛ አለመሆን ተግባራዊ ለመሆን አልቻለም። በየካቲቱ አብዮት የዲሞክራሲ ጭላንጭል ቢታይም፣ በአንድ በኩል በራሱ የግራ መፈክርን አንስቶ በሚታገለው ኃይል የርስ በርስ ሽኩቻና፣ በሌላ ወገን ደግሞ የወታደሩ አገዛዝ ብቸኛው ኃይል ሆኖ ከወጣ በኋላ የየካቲቱን ጥያቄዎች፣ በተለይም የዲሞክራሲን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ደብዛው እንዲጠፋ በማድረጉ የህዝባችንን ዕድገት ገቶታል፤ ነፃነቱንም እንዳለ ገፎታል። የህዋሃት አገዛዝ ስልጣን ከያዘ በኋላ ቢያንስ በጽሁፍ ደረጃ ሊገለጽ የሚችል የዲሞክራሲ መብት ቢኖርም፣ ሰራተኛውም ሆነ ገበሬው በራሱ ተነሳሽነት የመደራጀትና መብቱን የማስጠበቅ ነፃነት አልነበረውም። በተለይም ከምርጫ 1997 ዓ.ም በኋላ አገዛዙ የበለጠ ጨቋኝ እየሆነ በመምጣት ህዝባችንን ፍዳውን ሲያሳየው፣ አደገኛ ናቸው የሚላቸውን ደግሞ እስር ቤት ሲወረውርና የተቀረውን ደግሞ አፍኖ በመውሰድ ዱካቸው እንዲጠፋ ለማድረግ በቅቷል። የቀደሙትም ሆነ የዛሬው የወያኔ አገዛዝ ይህንን ያደረጉትና የሚያደርጉት ህዝብን በመፍራታቸው ነው። ህዝቡ ከነቃና ካወቀ ይጠይቀናል፤ ለመብቱም መረጋገጥ ይታገላል ብለው በመፍራታቸው ዲሞክራሲያዊ መብቶችን እንዳለ አፍነዋል። በዲሞክራሲ እጦት የተነሳ ህብረተሰብአዊ መዘበራረቅ እንዲፈጠር አድርገዋል። የአገራችን ዕድገት የኋሊት እንዲጓዝ ተገዷል።

እንደሚታወቀው የዲሞክራሲ ጥያቄ ከምርጫ ጋር ብቻ የሚያያዝ ሳይሆን ሰፋ ባለ በሁሉም መልክ በሚገለጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ኢንስቲቱሽናዊ ግንባታ ጋር የሚያያዝ ነው። የዲሞክራሲ ጥያቄ ከዚህ አልፎ በመሄድ በተለይም የመሬትን ጥያቄ ፍትሃዊ በሆነ መልከ ማከፋፈል ጋር የሚያያዝ ነው። በተለይም መሬትና ውሃ እንዲሁም ከዚህ ጋር የተያያዙ ተፈጥሮአዊ ነገሮች በሙሉ ሰው ሰራሾች እንዳለመሆናቸው መጠን የጠቅላላው ህዝብ ሀብቶች ናቸው። አንድ መንግስት ወይም አገዛዝ ስልጣኑን በመጠቀም ከህገ-መንግስቱ ውጭ የሆነ ለተወሰኑ የህብረተሰብ ኃሎች ብቻና ለውጭ ከበርቴዎች መሬት እየሸነሸነ የመስጠት መብት የለውም።

ለማንኛውም በተለይም ሃሳብን ሳይፈሩ ሳይቸሩ መግለጽ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ፣ በነፃ መደራጀት፣ ካለምንም ማስረጃ አለመታሰርና ከዚህ ጋር የተያያዙ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች በሙሉ መፈታት ያለባቸው ጉዳዮች እንጂ በሆነው ባልሆነው ምክንያት የሚስተጓጉሉ አይደሉም።

                                                                             9

ለአፍሪካ ህዝብ ዲሞክራሲ አያስፈልገውም፤ መጀመሪያ ዕድገት ነው የሚያስፈልገው የሚለው በሳይንስ ያልተደገፈ አባባል ዲሞክራሲ ሁሉ-ገብ በሆነ የአገር ግንባታ ላይ ሊኖረው የሚችለውን ከፍተኛ ሚና ካለመገንዘብ የተነሳ የሚሰነዘር የአላዋቂዎች አነጋገር ነው። በተለይም በአገራችን ሁኔታ ባለፉት 40 ዓመታት ያህል ከዲሞክራሲ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ በህዝባችን ላይ የደረሰውን መጠነ-ሰፊ የሆነ የአካልና የህሊና መጎሳቆል ስንመረምር የዲሞክራሲያዊ መብቶች ካለምንም ገደብ ተግባራዊ መሆን አለባቸው። ቅድሚያ የሚሰጠው እንጂ ውሎ የሚያድር አይደለም። በተለይም የወያኔን የመርዝ አገዛዝና በህዝብ ዘንድ ያሰራጨውን የመጠላላትና የመጠራጠር መንፈስ ማዳከምና የመጨረሻ መጨረሻም ማውደም የምንችለው ዲሞክራሲያዊ መብቶች ካለምንም ገደብ ተግባራዊ ሲሆኑ ብቻ ነው። የዶ/ር አቢይ አህመድ አገዛዝ የህንን ተገንዝቦ ተግባራዊ የማያደርግ ከሆነ ህዝቡ ራሱ ራሱን በማደራጀትና ሃሳቡን በጽሁፍም ሆነ በሃሳብ በመግለጽ መብቱን ማስጠበቅ ይኖርበታል።

ከዚህ አጠቃላይ ሁኔታ ስንነሳ ለሰላምና ለዲሞክራሲ ጠንቅ የሆኑ ነገሮች በሙሉ ቀስ በቀስ መወገድ አለባቸው። 1ኛ) ኮማንድ ፖስቱ መነሳት አለበት። 2ኛ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት አለበት። 3ኛ) ደህነነት ወይም ሴኩሪቲ እንዳለ መፍረስ አለበት። ከህዋሃት ጋር ግኑኝነት የሌላቸው ሰዎች ብቻ የጠቅላይ ሚኒስተሩን ህይወት መጠበቅ አለባቸው። እነዚህ እንዳሉ በጠቅላይ ሚኒስተሩ ትዕዛዝ የሚንቀሳቀሱና ተግባራቸውን የሚፈጹሙ ናቸው። ከዚህ በተረፈ እንደ ኢትዮጵያ የመሰለ ደሃ አገር ትልቅ የደህንነት መስሪያ ቤት አያስፈልጋትም። እንደዚህ ዐይነቱ መስሪያ ቤት የአገርን ሀብት ከመጋራትና ከማውደም በስተቀር ለህዝቡ ደህንነት የሚያመጣው ፋይዳ የለም። የተቋቋመውም የገዢዎችን ደህንነትና ሀብት ለመከላከል እንጂ የአገርን ብሄራዊ ነፃነት ለማስከበርና የውጭ ኃይሎችን ሴራ ለማክሸፍ አይደለም። እንዲያውም በተቃራኒው የአገርን ደህንነት የሚያቃውስና ብሄራዊ ነፃነትን የሚያስገፍፍ ነው። 4ኛ) የአጋዚ ጦር እንዳለ መፍረስ አለበት። ምስኪኑን ህዝብ፣ በተለይም ህፃናትንና እርጉዝ ሴቶችን ሁሉ ሳይቀር በጭፍን የሚገድል እስካሁን ድረስ መቆየቱ በጣም የሚያሳዝን ነው። አዛዦቹም ተጠያቂ አለመሆናቸው የሚያበግነን ጉዳይ ነው። ስለሆነም የወያኔን የበላይነት ለመጠባበቅ የተቋቋመው የህዝብና የአገር ጠላት የሆነው የግዴታ በአስቸኳይ መፈራረስ ያለበት ነው። 4ኛ፟) የወያኔ ጄኔራሎች እንዳሉ መነሳት አለባቸው። በተማሩና ከተለያዩ ብሄረሰቦች በተውጣጡ መተካት አለባቸው። አንድ ጄነራል ቢያንስ የማስትሬት ዲግሪ ያለው ሲሆን፣ በፍልስፍናና በሳይንስ እንዲሁም በቲዎሪ የሰለጠነ መሆን አለበት። ይህ ዐይነቱ ዕውቀት የማሰብ አድማሱን ከማስፋቱም ባሻገር ብሄራዊ ባህርዩን ያዳብረዋል። ኃላፊነቱና ግዴታው ህገ-መንግስትን ማክበርና ብሄራዊ ነፃነትን ማስጠበቅ መሆኑን ይረዳል። 5ኛ) የህግ አስፈጻሚው መስሪያ ቤት ፍትህን ተግባራዊ በሚያደረጉና በማያዳሉ ሰዎች መተካት አለበት። ፍርድ ቤትም ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ መሆን አለበት። 6ኛ) የወያኔ የቅስቀሳ መሳሪያዎች የሆኑ የራዲዮና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች በሙሉ ፖለቲካ ግኑኝነት በሌላቸውና ነፃ በሆኑና በፕሮፌሽናል ሰዎች መተካት አለበት። 7ኛ) እንደ ኢፈርትና ሜቴክ የመሳሰሉት የወያኔን ጡንቻ የሚያጠነክሩና የህዝብን ሀብት የሚዘርፉ ድርጅቶች በመንግስት ቁጥጥር ስር በመዋል፣ አንዳንዶቹ ወደፊት ወደ ግል የሚዘዋወሩበት ሁኔታ መዘጋጀት አለበት። እንደሜቴክ የመሳሰሉት ደግሞ ዕውቀቱ ባላቸው፣ ማለትም መካኒካል ኢንጂነሪንግ፣ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ፣ የዲዛይን ኢንጂነሪንግ ዕውቀት ባላቸውና በቴክንሽያኖች የሚመራና የሚንቀሳቀስ መሆን አለበት። በተጨማሪም እንደሜቴክ የመሰለ ድርጅት የራሱ የመመራመሪያ ጣቢያና በቂ የላቮራቶሪ መሳሪያዎች እንዲኖሩት ያስፈልጋል።

                                                                             10

ከተቻለ ድርጅቱ ቴክኖሎጂ ነክ ከሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየተባበረና ሃሳብ ለሃሳብ እየተለዋወጠ መስራት አለበት። በተለይም ሜቴክ የመንግስት አካል በመሆን ግን ደግሞ ከፖለቲካ ተፅዕኖና ቁጥጥር ውጭ በአውቶነመስ ደረጃ የሚተዳደር መሆን አለበት። ቦርዱም እንዳለ በመፍረስ በማኔጅሜንት ደረጃ የሚተዳደር መሆን አለበት። ማኔጅሜንትና የተለያዩ አካሎች ኃላፊዎች ብቻ ለኩባንያው በብቃትነት መንቀሳቀስ ተጠያቂ ይሆናሉ። የመዋዕለ-ነዋይ ክንውንን፣ ትርፍን በሚመለከትና እንደገና መልሶ መላልሶ ለመዋዕለ- ነዋይ ማዋል የማኔጅሜንቱ ኃላፊነት መሆን አለበት። ማኔጅሜንቱ እንደየሁኔታው እያየ በዐመት ከሚገኘው ትርፍ ውስጥ የተወሰነውን ለመንግስት ባጀት ማሟያ የሚሆን ገንዘብ ማስተላለፍ ያስተላልፋል። በዚሀ መልክ በመንግስትና በማኔጅሜንት መሀከል መተሳሰብና መተጋገዝ ካለ፣ እንዲሁም ማኔጅሜንቱ ግዴታውን የሚወጣ ከሆነ የቴክኖሎጂ ዕድገትን ማፋጠን ይችላል። 8ኛ) የአገራችንን የዛሬውንና የመጭውን ሁኔታ፣ እንዲሁም የሚቀጥለውን ትውልድ ዕድል በሚመለከት ሰፋ ያለ መድረክ በመክፈት መወያየትና መከራከር አለብን። ሜዳው ለጥቂቶች ብቻ መለቀቅ የለበትም። ስለለዲሞክራሲ የምናወራ ከሆነ የአገራችንን ሁኔታ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሁሉ በሳይንስና በምሁራዊ መልክ መወያየትና ወደፊትም ወጥተን ለህዝብ ማስተማር አለብን። ለምሳሌ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችና ፖሊሲዎችን፣ እንዲሁም ሁለ-ገብ ዕድገትን በሚመለከት፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂን ጉዳይ፣ ስለከተማዎችና መንደሮች ግንባታ፣ ስለቤት አሰራር ቴክኖሎጂና ከአገራችን ህዝብ ፍላጎት ጋር የሚሄድ የቤት አሰራር ዘዴ፣ ስለብሄራዊ ነፃነትና ስለውጭ ኃይሎች ሚና፣ ስለውጭ መዋዕለ-ነዋይ (Direct Investment) ጥቅምና ጉዳትን በሚመለከት፣ ስለ ዕርዳታ ድርጅቶች ሚናና፣ ስለሚያመጡት ጥቅምና ጉዳት፣ ስለማህብረሰብና ስለአካባቢ ጉዳይ… ወዘተ. … ወዘተ. በመሳሰሉት ነገሮች ላይ ሁሉ መከራከር አለብን። በዚህ መልክ በድፍረት ለመከራከርና ለመወያየት ዝግጁ ከሆን ለዲሞክራሲ ያለን ግንዛቤ ከፍ ያለ ነው ማለት ነው። ሃሳባችንንም ግልጽ ልናደርግ እንችላለን። ህዝቡም የትኛው ምሁር ለዕውነተኛ ዲሞክራሲና ዕድገት እንደቆመና የሚያመረቃም መፍትሄ እንዳለው ሊረዳ ይችላል። በአንፃሩ ግን በደፈናው የምንታገለው ለሊበራል ዲሞክራሲ ነው ብለን ነገሮችን አድበስብሰን የምናልፍ ከሆነና፣ በተለይም ደግሞ መድረኩ ለአንዳንድ ግለሰቦች ብቻ ክፍት የሚሆን ከሆነ እንዲያውም ዲሞክራሲንና ነፃነትን አዳፈን ማለት ነው። ስለሆነም በድፍረት ወጥተን ለመከራከር እንሞክር።

ያም ሆነ ይህ የሰላም መስፈንና የዲሞክራሲያዊ መብቶች ተግባራዊ መሆንና እነዚህን የሚቀናቀኑ የመወገዳቸው ጉዳይ ውሎ የሚያድሩ ጉዳዮች አይደሉም። ቀስ በቀስ በስራ ላይ መዋል ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው። ወደፊት መራመድና ውጭ አገርም ያለው ኢትዮጵያዊ አገሩ ገብቶ ሊያስተምርና በመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ ውስጥ ሊሳተፍ የሚችለው በአገር ውስጥ አስተማማኝ ሁኔታ ሲፈጠር ብቻ ነው። በወያኔ ማጅራች መቺዎች ህይወቱ የሚቀነጠስ ከሆነ ሌላው ለመግባት ይፈራል። ስለሆነም ለአገሩ ዜጋም ሆነ ከውጭ ወደ ውስጥ ለመግባት ለሚፈልገው ሁሉ አስተማማኝ ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው። መልካም ግንዛቤ !!

                                                                                           11

fekadubekele@gmx.de

Share on FacebookTweet about this on TwitterShare on Google+Share on RedditShare on TumblrBuffer this pageEmail this to someonePrint this page